ገፅታችን

ቆይታ

ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ይታይ የነበረውን የትራፊክ ማኔጅመንት ሲቋቋም የማኔጅመንቱ ዋና የሥራ ሂደት ኃላፊ ሆነው ከአለም ባንክ በተገኘ ጥናት መነሻነት የፓርኪንግ አጠቃቀም የትራፊክ ፍሰትና ሌሎች እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ ከፖሊስና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ሰርተዋል፡፡ በፌደራል ትራንስፖርት ሚንስቴር የሚንስትሩ አማካሪ ሆነው ለረጅም አመት አገልግለዋል፡፡


በአዲስ አበባ ከተማ ይታይ የነበረውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ ስራውን የጀመረው ፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች የትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ሲቋቋም ተቋሙን በዋና ስራ አስኪያጅነት እንዲመሩ የተመደቡት በግንቦት ወር 2006 ዓ.ም ነበር፡፡
ከነሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ ፣ ከነአቶ ካሳሁን ኃ/ማርያምና ከሌሎችም የድርጅቱ ባለውለታዎች ጋር በመሆን በትራንስፖርት ሚንስትር በተሰጣቸው ትንሽ ቢሮ ውስጥ ሆነው ነበር ስራቸውን የጀመሩት፡፡ መንግስት ሊሰጥ ያቀደውን የትራንስፖርት አገልግሎት ያላመኑ ሰዎች እንደነበሩ የሚያስታውሱት አቶ ደረጀ ወ/ዮሐንስ በወቅቱ ከጎናቸው ከነበሩ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን ባልተሟላም ሁኔታም ቢሆን ስራቸውን ጀምረው ዛሬ ብዙ ሰራተኛ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆኖ ሲመለከቱ የሚሰማቸው ደስታ ወደር እንደሚያጣ ይገልፃሉ ፡፡ የድርጅቱን የአንድ ዓመት ክንውንም ከካፒቴኖች ምልመላ ጀምሮ እንደሚከተለው ገልፀውልናል፡፡ ገፅታችን
ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ይታይ የነበረውን የትራፊክ ማኔጅመንት ሲቋቋም የማኔጅመንቱ ዋና የሥራ ሂደት ኃላፊ ሆነው ከአለም ባንክ በተገኘ ጥናት መነሻነት የፓርኪንግ አጠቃቀም የትራፊክ ፍሰትና ሌሎች እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ ከፖሊስና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ሰርተዋል፡፡ በፌደራል ትራንስፖርት ሚንስቴር የሚንስትሩ አማካሪ ሆነው ለረጅም አመት አገልግለዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ይታይ የነበረውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ ስራውን የጀመረው ፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች የትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ሲቋቋም ተቋሙን በዋና ስራ አስኪያጅነት እንዲመሩ የተመደቡት በግንቦት ወር 2006 ዓ.ም ነበር፡፡
ከነሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ ፣ ከነአቶ ካሳሁን ኃ/ማርያምና ከሌሎችም የድርጅቱ ባለውለታዎች ጋር በመሆን በትራንስፖርት ሚንስትር በተሰጣቸው ትንሽ ቢሮ ውስጥ ሆነው ነበር ስራቸውን የጀመሩት፡፡ መንግስት ሊሰጥ ያቀደውን የትራንስፖርት አገልግሎት ያላመኑ ሰዎች እንደነበሩ የሚያስታውሱት አቶ ደረጀ ወ/ዮሐንስ በወቅቱ ከጎናቸው ከነበሩ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን ባልተሟላም ሁኔታም ቢሆን ስራቸውን ጀምረው ዛሬ ብዙ ሰራተኛ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆኖ ሲመለከቱ የሚሰማቸው ደስታ ወደር እንደሚያጣ ይገልፃሉ ፡፡ የድርጅቱን የአንድ ዓመት ክንውንም ከካፒቴኖች ምልመላ ጀምሮ እንደሚከተለው ገልፀውልናል፡፡

ምልመላና የባስ ካፒቴኖች መረጣ

ምልመላና የባስ ካፒቴኖች መረጣ
የምናገለገለው ህዝብን ነው፡፡ የዩኒቨርስቲ መምህራን ፣ የጤና ባለሙያዎች ፣ የአስተዳደር ሰራተኞች በአጠቃላይ በተለያዩ የሙያ መስክ ላይ የተሰማሩ የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞችን ነው፡፡ እነዚህ ተገልጋዮች በሀገራችን ሁለንተናዊ ዕድገት ላይ ትርጉም ያለው ስራ የሚሰሩ ዜጐች ናቸው፡፡ በመሆኑም እነዚህን ሰራተኞች ለማገልገል የሚችል በስራ ልምድና ብቃቱ የተመሰከረለት በተለይ ለህግና ለደንብ ተገዥ የሆነ፣ ለሚያገለግለው ህዝብ ያገልጋይነት ቁርጠኝነት ያለው ሰራተኛ ሊሆን ግድ ነው፡፡
በመሆኑም እነዚህን የባስ ካፒቴኖች ለመምረጥና ወደ ስራ ለማሰማራት ከፍተኛ ትኩረት ማድረግ እንዳለበት አምነን ነው ወደ ስራ የገባነው፡፡
በቅድሚያ ባስ ካፒቴኖቻችን ያላቸው የስራ ልምድ ብቃትና ችሎታ ይጠናል፡፡ ቀደም ሲል በምን አይነት ስነ ምግባርና ሁኔታ የማሸከርከር ስራቸውን ይወጡ እንደነበር እናጠናለን፡፡ በተለይ በህዝብ ማመላለሻ አገልግሎት ስራ ላይ ለተሰማሩ ካፒቴኖች ቅድሚያ እንሰጣለን፡፡ ራሣቸውን፣ የሚያገለግሉትን ህዝብና የሚይዙትን በውድ ዋጋ የተገዛ ተሸከርካሪ ከአደጋ ጠብቀው ይጓዙ ዘንድ በቀደመው የስራ መስካቸው የነበራቸውን ከአደጋ የተጠበቀ ታሪክ በስፋት እንመረምራለን፡፡ ከዚያ በመቀጠል ለሚሰጡት አገልግሎት ኃላፊነት ይሰማቸው ዘንድ የቤተሰብ ኃላፊ መሆናቸውን እንመረምራለን፡፡ ለቤተሰቦቻቸው ያላቸውን አሳቢነትና ተቆርቋሪነት እንመዝናለን፡፡ ይህ ሁሉ በቃለ መጠይቅና በተለያዩ ዘዴዎች ከፈተሽን በኋላ ወደ ጤና ምርመራው ነው የምንገባው፡፡ ከማሸከርከር ባለፈ ቁጥሩ በርካታ የሆነን ተገልጋይ ለማስተገናገድ ያስችለዋል ተብሎ በህግ የተቀመጠውን የጤና ምርመራ ከፌደራል ፖሊስ ሆስፒታል ጋር በመተባበር እናስመረምራለን፡፡ ከዚህ ባሻገር ከተለያዩ ደባል ሱሶች ነፃ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ የነበራቸውን የስራ ልምድ ስንፈትሽም ቀደም ሲል ሲያሸከረክሩ የነበረው ተሸከርካሪ አይነትና ባህሪን እንመረምራለን፡፡ ለምሣሌ ከባድ የጭነት መኪና ማሸከርከርና ህዝብን ማጓጓዝ ፣ ከተማ ውስጥና ገጠር ማሸከርከር ፣ ከተማ ውስጥ ሆኖ በጣም በተጨናነቀ ቦታና ብዙ ግርግር በሌለባቸው ቦታዎች ማሸከርከር ልዩነት አለው፡፡ በዚህም መነሻነት ከስራችንና ከድርጅቱ አላማ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው ብለን የምናምንባቸውን በጥንቃቄ እንመርጣለን፡፡
በዚህ ሂደት ላይ ድርጅቱ ያቋቋማቸው የቴክኒክ ኮሚቴዎች ናቸው በህብረት በመሆን ቀጠራውን የሚያከናውኑት፡፡ ከአድሎ ፣ ከዘመድ ስራና ከእውቅና የፀዳ ይሆን ዘንድ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡
ስልጠና
ያላቸው የስራ ልምድ ብቃትና የአገልግሎት ብቃት ማረጋገጫ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ከላይ የዘረዘርነውን መስፈርት ያሟሉትን ቀጥታ ወደ ስራ አናሰማራቸውም፡፡ አውቶብሶቻችን ዘመናዊና አዲስ ምርት በመሆናቸው ስለሚያሸከረከሩት ተሸከርካሪ በቂ እውቀት እንዲኖራቸው ማንዋል በLCD ተዘጋጅቶ በቀላል አቀራረብ በሚገባቸው ቋንቋ በቡድን ከፋፍለን ስለተሸከርካሪቻችን ውጫዊና ውስጣዊ አካል ስልጠና ይሰጣቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ወደ ተግባራዊ ልምምድ የምናልፈው፡፡ ቅድሚያ ልምድ ካላቸው ካፒቴኖቻችን ጋር ተደርበው በመውጣት በከተማችን በሁሉም አካባቢዎች እንዲያሸከረክሩ እናደርጋለን፡፡ በዚህ ጊዜ ብቃት ችሎታቸውና ህግ አክባሪነታቸው ተመዝኖ በቴክኒክ ኮሚቴው አማካኝነት የግምገማ ሰርተፌኬት ተሞልቶ ከመጣልን በኋላ ነው ወደ ቅጥር የምናመራው፡፡ ወደ ስራም ከገቡ በኋላ ወዲያው አንድ ሰው ብቻ ወደ አገልግሎት እንዲሰማራ አናደርግም፡፡ ሁለት ሁለት እየሆኑ ለሁለት ለሦስት ወር ያህል እየተቀያየሩ እንድያሸከረክሩ ነው የምናደርገው፡፡ ብቃት ያላቸው በህጉ መሠረት ራሣቸውን ችለው ስራቸውን እንዲሰሩ አናደርጋለን፡፡ የብቃት ችግር የታየባቸው ካሉ ደግመን ወደ ስልጠና መልሰን እናሰገባቸዋለን፡፡
ካሰማራናቸው በርካታ አውቶብሶችና ከምንሰጠው አገልግሎት አንፃር እስካሁን በተሸከርካሪዎቻችን ላይ የደረሰም ሆነ ያደረሱት አደጋ አነስተኛ ነው፡፡ ስራ እንደጀመርን አካባቢ ይደርሱ የነበሩት አደጋዎች ከአሁኑ ጋር ሲነፃፀር በመጠኑ የጨመረ ነበር፡፡ “ይህን የአደጋ መጠን እንዴት መቀነስ ይቻላል?” በሚል የድርጅቱ ማኔጅመንት አባላት ቁጭ ብለው በጥናት ላይ የተመረኮዘ ውይይት አካሄዱ፡፡
በዚህ ጊዜ የደረስንበት ውሣኔ የስራ ላይ ስልጠና አሰፈላጊ መሆኑን ነበር፡፡ የድርጅታችን መካኒክ ሾፌሮች በየዕለቱ አደጋ ያደረሰውንና ምንም አደጋ ያላደረሰውን ገጽ በገጽ ምንድን ነው ችግሩ በሚል በየቀኑ በአንድ ለ አምስት አደረጃጀት ውይይትና ግምገማ እንዲያደርጉ ሁኔታዎች ተመቻቹ፡፡ በዚህም አንዱ ከአንድ ልምድ እየቀሰመ ስህተቱን እያረመ በመምጣቱ የሚደርሱ ቀላል አደጋዎችን ሳይቀር መቀነስ ችለናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ድርጅቱ ከሚሰጣቸው ስልጠናዎች ባለፈ አሽከርካሪዎችን ከሚያሰለጥኑ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር አደጋን ተከላክሎ በማሸከርከር ላይ ያላቸውን ዕውቀት በየጊዜው እንዲሰጡ አድርገናል፡፡ በተጨማሪም ከአዲስ አበባ መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ጋር በመነጋገር በከተማዋ ውስጥ ስላለው አጠቃላይ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ስልጠና እንዲሰጥ አድርገናል፡፡ ከከተማዋ ትራፊክ ፖሊስ ጋር የጠበቀ ቁርኝት በመፍጠር በሃገራችን ውስጥ ስለሚከሰቱ አሰቃቂ የትራፊክ አደጋዎች፣ ስለትራፊክ ህግና ስለምልክትና ማመልከቻ በቂ እውቀት እንዲኖራቸው በየጊዜው በንድፈ ሃሣብና በተግባር የተደገፈ ትምህርታዊ ገለፃ እንዲደረግላቸው በማድረጋችን ተገልጋዮቻችን ከአደጋ ከመጠበቃችን ባለፈ ለትራፊክ አደጋ ሌላው ህብረተሰብ እንዳይዳረግ የበኩላችንን በመወጣት ላይ እንገኛለን፡፡
ከዚህ ባሻገር በካፒቴኖቻችን መካከል መልካም የስራ ውድድር እንዲኖር በማድረግ ከወር ወር ከአደጋ የተጠበቁ በስነ ምግባራቸው የተመረጡትን በመለየት የገንዘብ ማበረታቻና እውቅና እንሰጣለን፡፡ ችግር ያለባቸው አሸከርካሪዎችን በደረጃ እንዲቀጡ እናደርጋለን፡፡ ከስህተታቸው ተምረው ችግራቸውን መቅረፍ ያልቻሉትን ደግሞ ከስራ እስከማሰናበት የሚደርስ እርምጃ እንወስዳለን፡፡ ያለምንም አደጋ መልካም አፈፃፀም ያሳዩ ቅርንጫፎቻችንም በመለየት ዕውቅና እንሰጣለን፡፡

 

በሰውና በንብረት ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ

በሰውና በንብረት ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ
ምንም እንኳን ሃገራችን ለማንም በሚታይ መልኩ በእድገት ጐዳና ላይ ያለች፣ የአለም ሀገራት አይን ሁሉ ያረፈባት መሆኗ የተጋገጠ ቢሆንም ዛሬ ድረስ የሃገራችንን ስም በአለም አቀፍ ደረጃ በመጥፎ የሚያስነሳትን የትራፊክ አደጋ ለመከላከልና ለመቆጣጠር አልተቻላትም፡፡ በአነስተኛ የተሸከርካሪ ቁጥር ብዙ ሰው ከሚሞትባቸው ሃገራት ተርታ ነው ስማችን አየተጠራ ያለው፡፡ ይህ ደግሞ ሁሉም የድርሻውን ባለመወጣቱ የተከሰተ ችግር ነው፡፡ ዛሬ የምንሰማቸው ዘግናኝ አደጋዎች ምንጫቸው ይሄ ነው፡፡ በድርጅታችን ውስጥ ያሉ ባስ ካፒቴኖች ይህን የተረዱ ሊሆኑ ይገባል የምንለውም ለዚህ ነው፡፡
በተለይ ህዝባዊ አገልግሎት የሚሰጡ የኛን መሰል ድርጅቶች አደጋን ስለመከላከል ብዙ ሊሰሩ ይገባል፡፡ እኛ አገልግሎት የምንሰጣቸው በርካታ ህዝባዊ አገልግሎት የሚሰጡ ሰራተኞች ናቸው፡፡ በነዚህ ዜጐቻችን ላይ አደጋ ተከሰተ ማለት የሚፈጥረው ችግር ከፍተኛ ነው፡፡ በመሆኑም ለትራፊክ ህግ ተገዥ የሆነ ለእግረኛ ቅድሚያ የሚሰጥ ራሱንና ሌላውን ዜጋ ከአደጋ የሚጠብቅ ከተራ ስሜትና ከማን አለብኝነት የራቀ መሆኑን በየዕለቱ ትኩረት ሰጥተን እንገመግማለን፡፡ የሃገራችን ገጽታ ተገንብቶ ባለማወቅና ባለማስተዋል በየዕለቱ የሚፈሰውን የዜጐችን ደምና የሃገር ንብረት ከጥፋት ለማዳን የበኩላችንን እየተወጣን ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ አገልግሎት በሚሰጡበት ጊዜ በግልጽና በስውር ክትትልና ቁጥጥር እናደርጋለን፡፡
ከሁሉ በላይ ደግሞ ተቆጣጣሪው ተጠቃሚው ህብረተሰብ ነው፡፡ ተገልጋዩ ያየውን ጠንካራና ደካማ ጐን ወዲያው ሪፖርት ያደርጋል፡፡ የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኛው በአግባቡ ስራውን ይሰራ ዘንድ መንግስት ከፍተኛ በጀት መድቦ አገልግሎት እየሰጠው መሆኑን ስለሚረዳ ንብረቱን የሚጠብቀው ራሱ ተጠቃሚው ነው፡፡ የካፒቴኖቻችን የስራ እንቅስቃሴ የሚመዘነው ተጠቃሚው በመሆኑ በስልክና በአካል በመገኘት የሚሰጠን ጥቆማ ለስራችን መሳካት ከፍተኛውን እገዛ እያደረገልን ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ እስካሁን ያን ያህል የጐላ ችግር የለም፡፡ ከስንዴ መካከል እንክርዳድ እንዲሉ አልፎ አልፎ ችግሮች ሲያጋጥሙን እርምጃችን ፈጣንና አስተማሪ ነው፡፡

ተገልጋዮቻችን

ተገልጋዮቻችን
መንግስት ይህን አገልግሎት ለፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኛውም ሆነ ለህዝቡ እንድንሰጥ ሲወስን ከፍተኛ በጀት መድቦ ነው፡፡ እነዚህ አውቶብሶች በጥንቃቄ ከተያዙ ለበርካታ አመታት አገልጋይ ይሆናሉ፡፡ አብዛኛው ህዝብ ማለት ይቻላል ይህን ተረድቶ እንደራሱ ንብረት ነው የሚይዛቸው፡፡ ጥፋት እንኳን ቢያይ ዝም አይልም፣ ይቆጣጠራል ፣ ይገስፃል፡፡ አልፎ አልፎ አንዳንድ ግለሰቦች በተሸከርካሪዎቹ ወንበርና ግድግዳ ላይ አላሰፈላጊ ጥቃቅን ስህተቶችን ይፈፀማሉ፡፡ በስነ ምግባርም አንፃር መታወቂያ እንዲያሳዩ ሲጠየቁ ፈቃደኛ ያለመሆን ለህግና ለደንብ ተገዥ የማይሆኑ ሰዎች ያጋጥማሉ፡፡ ይሁን እንጂ ቁጥራቸው እጅግ ጥቂት ነው፡፡
በተረፈ የምንሰጠውን አገልግሎት በተመለከተ ከተጠቃሚውና ከባለድርሻው አካላት ጋር በጋራ ቁጭ ብለን ጠንካራና ደካማ ጎናችንን እንገመግማለን የሚሰጡን አስተያየቶች ከመቶ ዘጠና በላይ ገንቢዎች ናቸው፡፡ አሰራራችንን ከመገምገም ባለፈም መጠይቅ በማዘጋጀት ተገልጋይ በግልፅነት አስተያየቱን እንዲሰጥ አድርገናል፡፡ በዚህ መልኩም የተሰጡን ምላሾች እጅግ አበረታች ናቸው፡፡ ይህ ማለት ግን ሙሉ ነን ማለት አይደለም መሻሻል ያለባቸውን አሰራሮች እያሻሻልን መጠናከር ያለባቸውን አገልግሎት አቅም በፈቀደ መጠን እያጠናከርን የበለጠ አገልግሎታችንን በአዲሱ ዓመት እናሰፋለን እናሻሽላለን፡፡ ምክንያቱም አውቶቡሶቹም ሆኑ አገልግሎቱ የሕዝብና የሀገር ነውና ፡፡

ስነ-ምግባር

ስነ-ምግባር
የካፒቴኖቻችን ዋና መገለጫ እንዲሆን የምንፈልገው ስነ ምግባር ነው፡፡ ዩኒፎርማቸውን አስተካክለው ከመልበስ ጀምሮ የተሸከርካሪውን ንጽህና እስከመጠበቅ ከዚያም ባለፈ ለሚያገለግሉት ህዝብ የአገልጋይነት ስሜትና ፍቅር እንዲኖራቸው ያስፈልጋል፡፡ “በጠዋት እንደምን አደራችሁ መልካም የስራ ቀን ይሁንላችሁ” ብሎ ከመመኘት ጀምሮ ትዕግስት የተሞላበት መስተንግዶ እስከመስጠት ይደርሳል፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ሰዓትን አክብሮ ከመነሻ ስፍራ የመንቀሳቀስ የጊዜ አጠቃቀም ስነምግባር ከካፒቴኖቻችን እንጠብቃለን፡፡ ይሄ የባህልም ለውጥ ነው፡፡ ለጊዜ አጠቃቀም ዴንታ ቢስ ሆነን የምንቆጠርበትን አመለካከት ለመቀየር ድርጅታችን ተግቶ ይሰራል፡፡ ተገልጋያችን ደስ ብሎት ለስራ ዝግጁ ሆኖ ወደ ስራው እንዲሰማራና ለአገልግሎት ፈላጊው የነቃ ግልጋሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ግብረገብን የተላበሰ መስተንግዶ መስጠት አስፈላጊ በመሆኑ ነው ከምልመላ ጀምሮ ከፍተኛ ጥንቃቄ የምናደርገው፡፡ በዚህ ዙሪያ ከተገልጋዮቻችን ያገኘነው ግብረ መልስ በጣም አበረታች ነው፡፡ በቀጣይ ደግሞ የበለጠ የአቅም ግንባታ ስራ እንሰራለን፡፡ በዚህ አጋጣሚ ስነ ምግባር ለተላበሰው ህዝባችን ያለንን ታላቅ አክብሮት ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡
የምንሰጠው አገልግሎት ተገልጋዩን የትራንስፖርት አገልግሎት ከመስጠትም የላቀ ነው፡፡ ከመልካም አስተዳደር ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው፡፡ ተጠቃሚዎቻችን የፍትህ አካላት የአስተዳደር ሰራተኞች የጤና ባለሙያዎች የጉምሩክ ሰራተኞችን ጨምሮ በርካታ ከህብረተሰቡ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ቀደም ሲል በትራንስፖርት እጥረት ሳቢያ በተገልጋዩ ላይ ይደርስ የነበረውን እንግልት ቀንሰው ጠዋት በሰዓት ገብተው ስራቸውን በአግባቡ ሰርተው አገልግሎታቸውን ለተገልጋዩ ሰጡ ማለት በመልካም አስተዳደር በኩል ይታዩ ከነበሩ ችግሮች መካከል አንዱ ተቀረፈ ማለት ነው፡፡ ለዚህም ነው መንግስት ትኩረት ሰጥቶ አገልግሎቱ እንዲጀምር ያደረገው፡፡
በያዝነው የበጀት አመታዊ አገልግሎቱ በእጥፍ እንዲጨመር በርካታ ስራዎች አየተሰሩ ነው፡፡ በያዝነው መስከረም ወር ብቻ ሃያ አዳዲስ አውቶቡሶችን ከቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ይህ ተጨማሪ አውቶቡሶች ርክክብ ከዚህ በኃላ የሚቋረጥ አይሆንም ፡፡ ያን ጊዜ በአቅም ማነስ ምክንያት በተደጋጋሚ በደርጅቱ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችና ጥያቄዎች በቂ ምላሽ ያገኛሉ ፡፡ “አገልግሎቱ በቂ አይደለም የመሀል ከተማ ሰራተኞች ተጠቃሚ አይደሉም መጨናነቅ አለ ለከተማ ህዝብ አገልግሎት (ለታክሲ) በቂ ትኩረት አልተሰጠም ለሚሉና ለመሳሰሉ አስተያቶች ምላሽ በሚሰጥ መልኩ አከልግሎታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡”ህዝብን ለማገልገል አደራ የተቀበለ መንግስት ነውና ጐዶሎ በታየበት የመልካም አስተዳደር ቀዳዳዎች ሁሉ መፍትሔ ለማዘጋጀት በመዘጋጀቱ በቀጣይም ዘርፉ ተጠናክሮ አገልግሎት መስጠቱን ይቀጥላል፡፡

አንድ ለአምስት

አንድ ለአምስት
ይህን ሙያዊ አደረጃጀት በጀመርንበት ጊዜ በሰራተኞቻችን ላይ በነበረው የግንዛቤ ብዥታ ሳቢያ ብዙም ውጤታማ አልነበርንም፡፡ የኋላ የኃላ ግን ሁሉም ስላጋጠመው ችግር የሚወያይበት ልምድ የሚቀስምበትና ችግሮቹን ለይቶ መፍትሔ የሚጠቁምበት መሆኑን ስንገነዘብ ዛሬ በድርጅታችን የባህል ያህል ተይዟል፡፡ የሚጠበቀውን ያህል ነው ባይባልም ሁሉም በአንድ ለአምስት ተደራጅቶ የየዕለት ውሎውን ይገመግማል፣ ባጋጠሙ ችግር ላይ ይወያያል፡፡ ይህ ግልፀኝነትን ለማስፈን አቋራጭ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ በስነምግባር ደረጃ የታዩ ችግሮችን በጋራ መድረክ ነቅሶ ያወጣል፡፡ በስነ ምግባር ደረጃ የተሻሉ በስራ አፈፃፀማቸው ልቀው የተገኙትን ግንባር ቀደሞች መርጦ ያበረታታል፡፡ ምንም እንኳን በቀጣይ አጠናክረን የምንሄድበት ቢሆንም በተለይ በሙያ ዘርፎቻችን ላይ የአንድ ለአምስት አደረጃጀት ውጤቱ የሚታይና የሚጨበጥ እየሆነ በመምጣት ላይ ነው፡፡
በድርጅታችን የተመዘገበውና እየተመዘገበ ያለው ውጤት ባለቤት ተገልጋዩና ጨዋው ህዝባችን ነው፡፡ ድርጅታችን አገልግሎት በሰጠበት አንድ ዓመት ውስጥ የተናበበ የተሳካ ውጤት ሊመዘገብ የቻለውም ሁሉም ሰራተኛ እጅ ለአጅ ተያያዞ ባደረገው የሌት ከቀን ጥረት ነው፡፡ መንግስት ያቀደው ተሳክቶ ያለው የትራንስፖርት እጥረት በመጠኑ ተቀርፎ ያለእንግልትና ውጣ ውረድ ወደ ስራው የሚገባና ከስራው የሚወጣ የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኛ ማየት የቻልነው በጋራ ጥረታችን ነውና ድክመቶችን በማረም ጥንካሬዎቻችንን በማጐልበት አብራችሁ ለነበራችሁ ሁሉ እንኳን ለአንደኛው አመት የምስረታ በዓላችን በሰላም አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡
ሁሌም እንደምንለው ህዝብን ከማገልገል የላቀ ተግባር የለምና በቀጣይም የነበረንን ግንኙነት አጠናክረን ለሃገራችን ዕድገትና ስኬት በጋራ እንሰራለን፡፡ በሁሉም መስክ የተመዘገቡ ድሎቻችን ተጠናክረው ይቀጥሉ ዘንድ የጋራ ጉዟችን መሠረት ነውና መጪውን ጊዜ በተሻለ ያገልጋይነት ስሜት ለመስራት ድርጅታችን ዝግጁ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡