“ህዝብን ከማገልገል የላቀ ምን አለ?”

“ህዝብን ከማገልገል የላቀ ምን አለ?”

ብዙዎቹ የባስ ካፒቴኖቻችን የረጅም ጊዜ ልምድና የማሽከርከር ዕውቀት ያላቸው ናቸው፡፡ መኪና ማሽከርከር መቻል ብቻ በቂ ዕውቀት እንዳልሆነ በተጨባጭ በሚታይበት በዚህ አደጋ በበዛበት ዘመን ለህግ ተገዥመሆንና ከዚያም በላይ በሃላፊነት ስሜት ማሽከርከር ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል፡፡

በመዲናችን አዲስ አበባ ብቻ በትራፊክ አደጋ በአመት ብዙ መስራት፣ ለሀገርና ለወገን ብዙ መጥቀም እየቻለ ሳያስበው ድንገት እንደወጣ በየመንገዱ ይቀራል፡፡  ለሀገር ዕድገት ለልማት ቢውል በርካታ ትምህርት ቤቶች ጤና ኬላዎችና ልማቶችን መስራት የሚችል የሀገር ገንዘብ ካለችን የኢኮኖሚ አቅም ላይ በአመት በርካታብር በተሽከርካሪ አደጋ ይወድማል፡፡

በአለም አቀፍ ደረጃ በዕድገቷና በሰላማዊ የቱሪስት መዳረሻነቷ ስሟ እየገነነ ለመጣው ሀገራችን ይህ የትራፊክ አደጋ ለስሟ በመጥፎ መነሳት ዛሬ ዛሬ ብቸኛው ምክንያት እየሆነ በመምጣት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ የትሪፊክ አደጋ ግን ልንከላከለው የማንችለው የተፈጥሮ አደጋ አይደለም፡፡ ችግሩ ከአመት አመት እየዘለቀ ወሬውም ዜናውም እየተለመደ መምጣቱ የተፈጥሮ አደጋ ያህል እየመሰለ መጥቷል፡፡ አብዛኛው ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የእግረኛው ህግን ጠብቆ ያለመንቀሳቀስ ተጠቃሽ ይሁን እንጂ የአሽከርካሪዎች ህግን ያለማክበርና ሃላፊነት የጐደለው እንቅስቃሴ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል፡፡

በተለይም እንቅስቃሴና የትራፊክ ግርግር በበዛባቸው አዲስ አበባን በመሰሉ ከተሞች የአደጋው ቁጥር ያንኑ ያህል የበዛ ነው፡፡ ይህን ለሀገራችን የገፅታ ግንባታ ፈተና እየሆነ የመጣውን የትራፊክ አደጋ ለመቆጣጠርና ለመከላከል መንግስት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ቢሆንም ችግሩ የአመለካከት ለውጥን የሚፈልግ፣ ለራስና ለሌላው ህይወት ዋጋ ሰጥቶ ማሽከርከርን የሚጠይቅ በመሆኑ የችግሩ መጠን ለሳምንታት ሲቀንስ በሌላ ሳምንት ደግሞ ቁጥሩ እጅግ ሲያሻቅብ ይኸው ዛሬ ድረስ ደርሷል፡፡

ከሀገራችን አልፋ የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ የበርካታ አለም አቀፍ ተቋማትና የበርካታ ዲኘሎማቶች መቀመጫ የመሆኗን ያህል በዘመነ አስተሳሰብና አመለካከት ከጊዜ ወደ ጊዜ መፍትሄ ያልተገኘለትን አደጋ መከላከል ካልቻልን ችግሩ እያባሰ ሄዶ መልካም ስሟን ጥላሸት እየቀባ የሚቀጥል ይሆናል፡፡በተለይ ህዝባዊ አገልግሎት የሚሰጡ የህዝብ ማመላለሻዎች ከሚያገለግሎት የህዝብ ቁጥር አንፃር አደጋ ቢከሰት የሚደርሰውን ውድመት ተረድተው ለህግና ለሰብአዊነት ቅድሚያ ሰጥተው ለአገልግሎት ካልተዘጋጁ ለአደጋው መበራከት የሚኖራቸው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡

ከዚህም ባሻገር የሚያገለግሎት ህዝብ የሀገር እድገት መሰረት መሆኑን ተረድተው ስነምግባር በተላበሰ መንፈስ በአገልጋይነት ስሜት ስራቸውን መሸፈን ካልቻሉ የታሰበው ህዝባዊ አገልግሎት ይሳካል ተብሎ አይታመንም፡፡ ለዚህ ነው የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት የባስ ካፒቴኖችን ሲመርጥ እጅግ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ምልመላውን የሚያከናውነው፡፡በልምምድና በችሎታ የተካኑ በስነምግባራቸው ምስጉን የሆኑትን በመብራት በመፈለግ የድርጅቱ አባል እንዲሆኑ ይጋብዛል፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ለህግ ተገዥ፣ ለሚያገለግሉት ህብረተሰብ ተገቢውን ክብርና አገልግሎት የሚሰጡ እንዲሆኑ የህግም የህሊናም ግዴታ ይጣልባቸዋል፡፡

ስራቸው ከተራ ሹፍርና ወይም ከማሽከርከር አገልግሉት የላቀ መሆኑን ለመግለፅ ነው “ባስ ካፒቴን” የሚለውን የማዕረግ ስም እንዲሰጣቸው የተወሰነው፡፡ ማለዳ ተነስተው ተሽከርካሪዎቻቸውን አፅድተው የክብር ልብሳቸውን አስተካክለው ወደ ስራ ገበታቸው በመሄድ ዝግጁ ሆኖ የሚጠብቃቸውን የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኞች በሰዓቱ ደርሰው በክብር ካስገቡ በyላ “እንደምን አደራችሁ ክቡራን መንገደኞቻችን” በሚል ካፒቴናዊ ስነስርዓት የዕለቱን ስራቸውን ይጀምራሉ፡፡ ተሳፋሪዎች ቀበቶ እንዲያስሩና በአግባቡ መቀመጣቸውን እንዲያረጋግጡ ከጠየቁ በኋላ “መልካም የስራ ቀን ይሁን ዛሬ ደስ የሚል ቀን ነው”፡፡ ብለው ጉዟቸውን ይጀምራሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ደስ የሚለው የስራ ቀን ይጀመራል፡፡ ስራቸው ህዝብን ማገልገል ነውና ተገልጋዩ ሲደሰትና ሲረካ ከማየት የበለጠ ደስታ ለነሱ ብዙም የለም፡፡

ተገልጋዮቻቸው የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ስመጥር የሆኑ የዩኒቨርሲቲና የኮሌጅ መምህራን፣መልካም አስተዳደር ለማስፈን የሚሰሩ የህግ ባለሙያዎች፣ የፖሊስ አባላት፣ በተለያዩ የመንግስት ሆስፒታሎች የላቀውን የሰውን ህይወት የመታደግ ስራ የሚሰሩ ዶክተሮችና የጤና ባለሙያዎች፣ የክፍለ ከተማና የወረዳ አመራሮች ፣የጉምሩክና የገቢዎች ሰራተኞች እና ሊሎችም በርካታ ህዝብ አገልጋዮች መሆናቸውን የሚረዱት የባስ ካፒቴኖቻችን ስነምግባርን የተላበሰ አገልግሎት በመስጠት በየቢሮው ለሚጠብቃቸው ህዝብ በአግባቡ ለማድረስ ዘወትር ይተጋሉ፡፡ከሺህ አንድ አይጠፋምና ሰዓት ማርፈድ፣ህግን ያልተከተለ ማሽከርከር፣ስነምግባር የጐደለው መስተንግዶ በሚያጋጥምበት ጊዜ ባለቤቱ ተገልጋዩ ነውና ሳይውል ሳያድር ወድያውኑ ችግሩን በማስረጃ አስደግፎ ወደ አመራሩ ስለሚያደርስ አስቸኳይ የመፍትሄ ርምጃ ይወሰዳል፡፡በርግጥ ህዝብን ከማገልገል የላቀ ተግባር የለምና በዕድሜአቸው የሰከኑ በልምድ የተካኑ ካፒቴኖች በዘወትር ስራቸው የተመሰገኑ ናቸው፡፡ የድርጅቱ አባል ከመሆናቸው በፊት የገቡትን የውዴታ ግዴታ ጠብቀው ታዛዥና ቅን አገልጋይ ሆነው ከተገልጋዬቻቸው ጋር ዝምድናንና ጓደኝነትን ተላብሰው አንድ አመት ሙሉ ተጉዘዋል፡፡ አገልግሎቱ ተጠናክሮ የሚቀጥል ልማታዊ ለሰራተኛው ቅን አሳቢ ከሆነ መንግስት የሚጠበቅ በመሆኑ በቀጣይም ጐዶሎው ሞልቶ ጠንካራው እያየለ ህዝባዊ አገልግሎቱ ይቀጥላል ፡፡ “በርግጥ ህዝብን ከማገልገል የላቀ ምን አለ”?

"ህዝብን ማገልገል በረከት  ነው"     ባስ ካፒቴን መኮንን ተጫኔ

 “ለረጅም አመታት በሹፍርና ሞያ ሰርቻለሁ ህዝባዊ አገልግሎት በሰጠሁባቸው አመታት በተቻለኝ መጠን በሃላፊነት ከአደጋ በተጠበቀ ሁኔታ ስራዬን ሳከናውን ቆይቻለሁ፡፡ የበርካታ ቤተሰብ አስተዳዳሪ በመሆኔ ለራሴና ለሌላው የተቆርቋሪነት ስሜት ይሰማኛል፡፡ ከዚህ በላይ ደግሞ በየጊዜው የማዳምጠው የትራፊክ አደጋ ዜና ያሳዝነኛል፡፡ “ለምን “ ብዬ ሁል ጊዜ እጠይቃለሁ፡፡ ይህን ህግን አክብሮ ማሽከርከር ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ያዳበርኩት ስነምግባር ነው፡፡ ህግን ጥሶ ያለአግባብ የሚያሸከረክር ሲያጋጥመኝ ለማስተማር ወደ yላ አልልም፡፡ የትም ለማይደረስ ተአምር የሚሰሩ ይመስል ለእግረኛ ቅድሚያ ሳይሰጡ የሚበሩ አሽከርካሪዎች ይገርሙኛል፡፡እኛ አገልግሎት የምንሰጠው ህዝብ ወገኖቻችን ናቸው፡፡ እናት፣ አባት ልጆቻችን ጭምር ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ተገልጋዮች ማክበር ለራስም ክብር ነው፡፡ ሰውን ካከበርነው ያከብረናል ከናቅከውም ደግሞ ያን ያህል ምላሹ ጥሩ እይሆንም፡፡አሁን በምስራው ስራ እጅግ ደስተኛ ነኝ፡፡ ከተማ ውስጥ ባለው የትራንስፖርት ችግር እጅግ አዝናለሁ፡፡ በአንፃሩ ደግሞ የተቸገረውን ህዝብ ሳገለግል በጊዜ ወደ ስራው ገብቶ በጊዜ ወደ ቤቱ ሲመለስ፣ ዕድሜ ይሰጣችሁ እያለ እኛንም መንግስትንም ሲመረቅ ሳይ ዕድሜዬ ይጨምራል፡፡ በረከት ይሞላኛል፡፡ ዕውነቴን ነው ህዝብን ማገልገል በቅንነትና በታዛዥነት መስራት በረከት ነው፡፡”

“ህብረተሰቡ ሊደሰት ሳይ ደስታዬ ወደር ያጣል” ባስ ካፒቴን ብዙአየሁ

”ከሁሉ በላይ ስራዬን የምጀምረው በድምፅ ማጉያ እንደምን አደራችሁ ብዬ ነው፡፡ ማታም ሲሆን ደህና እደሩ መልካም እረፍት ብዬ ነው ከወገኖቼ ጋር የምስነባበተው፡፡ ህዝቡ ደስተኛ ነው፡፡ ዘወትር ይመርቀናል ፣ይህ ደግሞ የበለጠ በስነምግባር ህዝብን እንዳገለግል ተጨማሪ ጉልበት ይሆነኛል፡፡ በተለይ ለመንግስት ሰራተኛው የሰጠነው አገልገሎት ከፍተኛ መሆኑ ይሰማኛል ቀደም ሲል ከቤት ወጥቶ በትራንስፖርት ችግር ሳቢያ አርፍዶ ወደ ስራ የሚገባው ተገልጋይ በዚህ የተነሳ የሚደርስበት መጉላላት እንዲቀንስ በማድረጋችን በግሌም እንደ ድርጅት አባልነቴ ኩራት ይሰማኛል፡፡ ህዝቡ እጅግ ጨዋ ነው፡፡ ከኛ በላይ ለአውቶብሶቹ ያስባል ይጠነቀቃል፡፡ አንዳንዴ ቀድመው የደረሱት አውቶብሶቹን ሲያፀዱ እመለከታለሁ የራሳቸው ሀብት መሆኑን በቃል ሳይሆን በተግባር ይገልፃሉ፡፡ አንዳንድ ጥፋት ሲመለከቱም ለምን ብለው የሚናገሩት አጥፊውንም የሚገሰፁ እነሱው ናቸው፡፡ ከመሀላቸው የተመረጡት ተቆጣጣሪዎች ለስራው መሳካት ያላቸው እገዛ ከፍተኛ ነው፡፡ በአጠቃላይ መንግስት ለዜጐቹ ይህን በማሰቡ ውጤቱንም በቅርበት ስለማየው ይገርመኛል፡፡ አንዳንዶች እንደሚገልፁልን ከደመወዝ ጭማሪ በላይ የሚደሰቱት በዚህ አገልግሎት ነው፡፡ ገንዘብም ይዘህ እኮ ትራንስፖርት ታጣለህ፡፡ከምናጓጉዛቸው ሰራተኞች ጋር ዝምድና ፈጥረናል በብዛት ሰው ይተዋወቃል ይከባበራል እኛንም ያከብሩናል፡፡ ስራዬን ሰርቼ ወደቤቴ ስገባ የሚሰማኝ ደስታ ወደር የለውም፡፡”

“ከማገኘው ደመወዝ የበለጠ የህዝቡ እርካታ ያስደስተኛል” ባስ ካፒቴን አማኑኤል አብርሃም

“ብዙው ተገልጋያችን ጨዋና የሚወደድ ነወ፡፡ በዚህ የትራንስፖርት ችግር ባለበት ወቅት በሰዓቱ ተገኝተን ወደ ስራው ቦታ ስናደርሰውና ስራውን ከጨረሰ በyላ ያለምንም መጉላላት ወደ ቤተሰቦቹ ስንቀላቅለው ደስታቸውንና እርካታቸውን የሚገልፁበት መንገድ ያጣሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ጥቂቶች ሰነምግባር የጐደለው ሁኔታ ያሳዩናል፡፡ በዚህ ጊዜ ትዕግስት ያስፈልጋል፡፡

መሳሳቱን አስረድተን ለቀጣይ ስህተቱን እንዲያርም እናደርጋለን፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ሌላው ተገልጋይ በመሃል ገብቶ ዳኝነቱን ይሰጣል፡፡ የተሳሳተው ወገን ወዲያው ስህተቱን አርሞ ወደ መስመር ይገባል፡፡አገልግሎቱን በማወቅም ይሁን በሌላ ሁኔታ ከስራ መግቢያና መውጫ ስዓት ውጭ ባለው ጊዜ በምንሰጠው የህዝብ ታክሲ አገልግሎት ብዙ ህዝብ እየተገለገለበት ነው ለማለት አያስደፍርም ምቾት ያላቸውን ባሶች ከፍተን መንገደኛው እንዲገባ ስንጠይቅ ተሰልፎ ታክሲ መጠበቅን የሚመርጥ ያጋጥመናል፡፡ ብዙው ሰው ለመንግስት ሰራተኞች ሰርቪስ ብቻ የምንሰጥ ይመስለዋል፡፡ በተመጣጣኝ ዋጋ የታክሲ አገልገሎት እንደምንሰጥ ተረድቶ ንብረቱ ስለሆነ ሊጠቀምበት ይገባል፡፡

ከዚህ በተረፈ የገባነው ግዴታ አለ፡፡ ለትራፊክ ህጐች ተገዥ ሆነን ለሀገር ልማትና ግንባታ የድርሻችንን በመወጣት ላይ ነን፡፡ ዳኛው በሰዓቱ ደርሶ ፍትህ ሊሰጥ፣ ዶክተሩ በጊዜ ወደ ስራው ተሰማርቶ የታመመን ሲያድን መምህሩ በስዓቱ ወደ ተማሪዎቹ ደርሶ ዕውቀቱን ሲያካፍል ከማየት ሌላ የሚያስደስት ተግባር የለም፡፡ ከማገኘው ደመወዝ የበለጠ ከህዝብ የማይገኘው ምስጋና ልቤን በደስታ ይሞላዋል፡፡ ካፒቴን አማኑኤል ብለው ሲጠሩኝም ደስ ይለኛል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ሁሉንም እንኳን ለአንደኛ አመት በአላችን በሰላም አደርሰን አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡”

“ቤተሰባዊ ዝምድናን መስርተናል” ባስ ካፒቴን ታሪኩ ከበደ

“ስራዬን ከጀመርኩ ጀምሮ የምሰራው ከገላን ስድስት ኪሎ ነው፡፡ የኛ አገልገሎት ከመጀመሩ በፊት በተለይ ሰራተኛው ምን ያህል እንግልት ይደርስበት እንደነበር አውቃለሁ፡፡ የምንሸፍነው ረጅም ርቀት በመሆኑ ተገልጋዩ አንድ ቀን አገልግሎቱን ቢያጣ ምን ያህል እንደሚቸገር ሁላችንም እንረዳለን፡፡ ተሳፋሪው በሰዓቱ ተዘጋጅቶ ይጠብቀናል፡፡ እኔም በሰዓቱ ደርሼ ወደ ስራ ገበታው አደርሰዋለሁ፡፡ አልፎ አልፎ መታወቂያ ለማሳየት ፍቃደኛ የማይሆኑ አሉ፡፡ ቢሆንም ጉዳዩን በመግባባት እናስተካክለዋለን፡፡

አገልግሎት ለመስጠት ከቤታችን የምንወጣው በጣም ማለዳ ነው፡፡ ይህ ለእኔ አስቸጋሪ ቢሆንም የህዝቡን ደስታ ሳይ ግን በጣም እደሰታለሁ፡፡ እኔ አንድ ነኝ የማጓጉዘው ግን ከስልሳ ሰው በላይ ነው፡፡ እና የብዙሀኑ ደስታ ከኔ ደስታ በላይ ያረካኛል፡፡ ያን ሁሉ ሰው ይዥ የምጓዘው እኔ በመሆኔ ህይወታቸውን ከአደጋ መጠበቅ እንዳለብኝ አውቃለሁ፡፡ ቅድሚያ መስጠት ለሚገባው ቅድሚያ በመስጠት ለትራፊክ ምልክትና ማመልከቻ ተገዥ በመሆን በስነምግባር የታነፀ አገልግሎት ለመስጠት እጥራለሁ፡፡ ከደንበኞቼ ጋር የቤተሰብ ያህል ነው አግባባችን ባህሪይ ለባህሪይ ስለምንግባባ ያን ያህል አስቸጋሪ ሁኔታ አያጋጥመንም፣አንድ አመት ሙሉ ተዋውቀናል፣ ተግባብተናል ቤተሰባዊ ዝምድናን መስርተናል ከመግባባታችን የተነሳ ማን የት ቦታ እንደሚጠብቀኝ፣ ማን እንደቀረ ማን እንደመጣ አውቃለሁ፡፡በአጠቃላይ በስራዬ ደስተኛ ነን ደንበኞቼም እንደዚያው፡፡”

“እርስ በእርሳችን የመማማር ልምድ አለን“ ባስ ካፒቴን----------

“አገልግሎት የምንሰጣቸው ለተለያዩ ባለሙያዎች ነው፡፡ አንዳንዱ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ነው ወደ ስራ የሚገባው ለምሳሌ መምህራንና የጉምሩክ ሰራተኞች ቶሎ ወደ ስራ መሄድን ይፍልጋሉ፡፡ ሌላው ደግሞ ሁለት ሰዓት ተኩል ወደ ስራ ስለሚገባ በጠዋት መነሳትን አይወድም፡፡ እነዚህን ሃሳቦች አስታርቆ ሁሉንም ለማስደሰት ትግዕስት የተሞላው ተግባር ያስፈልጋል፡፡ የኔ መስመር ከሳንሱሲ ቦሌ ነው በታቻለ መጠን መደበኛ የመነሻ ሰዓቴን ጠብቄ ቀድመው የመጡትን እያጫወትኩ በሰዓቴ እነሳለሁ፡፡ ሰራተኛው በአገልግሎቱ እጅግ ተጠቃሚና ደስተኛ ነው፡፡

ለረጅም አመታት የማሽከርከር ልምድ ስላለኝ ይህ ልምዴ ለአሁኑ ሰራዬ ጠቅሞኛል፡፡ ሰርዓት የሌላቸው አንዳንድ አሽከርካሪዎች ሲያጋጥሙኝ ከነሱ ጋር እልህ አልያያዝም የጫንኩት ህዝብ እንደመሆኑ መጠን የሚባክን ደቂቃ ሊኖር ስለማይገባ በትዕግስት በማለፍ ለአደጋው መቀነስ የድርሻዬን እየተወጣሁ ነው ብዩ አምናለሁ፡፡ ባለን የአንድ ለአምስት አደረጃጀት በስራችን ላይ ያጋጠሙንን ችግሮች ቁጭ ብለን እንወያያለን፡፡

አንዱ አንዱን ያስተምራል፣ የልምድ ልውውጥ እናደርጋለን ፣አገልግሎታችን የተሻለ ይሆን ዘንድ ይህ መድረክ ጠቅሞናል፡፡

ምንም እንኳን ስታሽከረክር ራስህ ብቻ ተጠንቅቀህ ከአደጋ መጠበቅ ባትችልም አደጋ ፈጣሪ አለመሆን ግን ትችላለህ፡፡ ያለን ልምድ ለዚህ ጠቅሞናል፡፡ በየጊዜው ድርጅታችን የሚሰጠን የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች አገልግሎታችን የተሻለ እንዲሆን አቅም እየፈጠረልን ነው፡፡”

“ህዝቡ በንብረቱ ሊጠቀምበት ይገባል“ የምስራች ገቢሳ (የአገልግሎት ገንዘብ ተቀባይ)

“ለዚህ ነዋሪ ስለምንሰጠው የነዋሪዎች የትራንስፖርት አገልገሎት በቂ ግንዛቤ አለን፡፡ የትራንስፖርት ችግር ባለበት ቦታ ሁሉ ከስራ ሰዓት መውጫና መግቢያ ውጭ በተመጣጣኝ ክፍያ አገልግሎት እንሰጣለን ፡፡ ይሁን እንጂ ብዙው ህዝብ ለመንግስት ሰራተኞች ብቻ አገልግሎት የምንሰጥ ሰለሚመስላቸው ወደኛ አይመጡም፡፡ ባለን አቅም ሰለአገልግሎቱ ገልፀን ወደኛ አውቶብስ እንዲመጡ እንጋብዛቸዋለን፡፡ አሁን አሁን የተሻለ ነው፡፡ይሁን እንጂ በቀጣይ በተሻለ ሁኔታ በተሻለ ምቾት የታክሲ አገልግሎት እንደምንሰጥ አውቆ ሊጠቀምበት ይገባል፡፡ በተረፈ ግንዛቤው ያላቸውና የሚጠቀሙት በጣም ደስተኞች ናቸው፡፡ በተለይ ረጅም ርቀት የሚጓዙ ተገልጋዬቻችን ዘወትር ደስታቸውን ይገልፁልናል፡፡ከበርካታ ሰዎች ጋር መሰራት የተለያየ ባህሪይ ያለውን ሰው እንድታገኝ ያደርግሃል አብዛኛው ጨዋ ቢሆንም አንዳንዱ ተጠቃሚ ያልተገባ ድርጊት ይፈፅማል፡፡ቢሆንም ስራዬ አገልግሎት መስጠት ስለሆነ በትዕግስት የተሳሳተውን አስተምራለሁ ፡፡ እኔም ያለብኝን ችግር መለስ ብዬ አያለሁ በዚህ የወጣትነት ዕድሜዬ ከእኔ በላይ የሆኑ እናቶችንና አባቶችን ማገልገል መቻሌ ደስታን ይሰጠኛል፡፡እነዚህ አውቶብሶች የማንም አይደሉም፣ የህዝቡ ናቸው፡፡ ህዝቡ በንብረቱ ሊጠቀምባቸው ግድ ነው፡፡ በቀጣይ እኛ የምንሰጠው አገልግሎት ከስራ ሰዓት መግቢያና መውጫ ውጭ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በመሆኑ እንዲጠቀምባቸው እጠይቃለሁ፡፡”

“ምቾት ባላቸው አውቶብሶቻችን ይጠቀሙ “ መቅደስ ታደሰ (የአገልግሎቱ ገንዘብ ተቀባይ)

“አንዳንድ ሰዎች ስለአውቶብስ አገልግሎት ያላቸው ግንዛቤ ዝቅተኛ ነው፡፡ በሰለጠነው አለም አብዛኛው ህዝብ በአውቶብስ እንደሚጠቀም እንሰማለን፡፡ እኛ ሀገር ደግሞ የተገላቢጦሽ ነው፡፡ ረጅም የታክሲ ሰልፍ ይዘው እኛ በምንጠራበት ጊዜ የማይገቡ ብዙ ሰዎች አጋጥመውኛል፡፡ ሁልጊዜ ይሄ ነገር ግርም ይለኛል፡፡በጠራራ ፀሐይ ረጅም ሰልፍን አይተን ወደነሱ ስንጠጋ በተለይ ቀደም ሲል እውነት የማይመስላቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ አሁን አሁን የተሻለ ቢሆንም የበለጠ ግንዛቤው ሊፈጠር ይገባል፡፡የአውቶብሶች ምቾች ከታክሲና ከሌሎች የህዝብ ትራንስፖርት አገልገሎት የተሻለ ነው፡፡ መኪኖቹ አዳዲስና ዘመናዊ ናቸው፡፡ በዚህ አገልግሎት ተጠቅሞ ጊዜንና ገንዘብን መቆጠብ ብልህነት ነው እላለሁ፡፡