ምላሽ ለሚሹ ጥያቄዎች

ምላሽ ለሚሹ ጥያቄዎች

ወደ ተለያዩ የፐብሊክ ሰርቪስ መስሪያ ቤቶችና ተቋማት ተንቀሳቅሰን የአንድ አመት ህዝባዊ አገልግሎታችን ምን ይመስል እንደነበር ለመጠየቅ ሞክረናል፡፡ ብዙዎች ቀደም ሲል ይደርስባቸው የነበረውን እንግልት መውደቅና መነሳት ወደ ኋላ እያሰቡ መንግስት ይሄንን መልካም ተግባር ለሰራተኛው አስቦ አገልግሎት መጀመሩ በስራ ህይወታቸውና በማህበራዊ ህይወታቸው ላይ ያመጣውን ለውጥ በተጨባጭ ምሣሌ እየጠቀሱ በምስጋና አውግተውናል፡፡ ከእነዚህም በላይ አገልግሎት ፈልጐ በየቢሮው ተኮልኩሎ ለሚጠብቃቸው ህዝብ በሰዓት ደርሰውና የዝግጅት ጊዜ አግኝተው ስራቸውን ማከናወናቸው ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እንዳገዛቸው ከሁሉ በላይ የተገነባ ስብዕና ይዘው ወደ ስራ ገበታቸው ለመሰማራት እንዳስቻላቸው ገልፀውልናል፡፡

አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎቻችን ግን “በሌሊት ከቤታችን ስለምንወጣ ልጆቻችንን በአግባቡ ማስተናገድ አልቻልንም” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ “በተለይ ባስ ካፒቴኖቹ በታክሲ ስራ ለሚያገኙት ጥቅም ሲሉ በሌሊት እንድንነሳ ያደርጉናል” ሲሉ አስተያየት የሰጡ ተገልጋዮች ምላሽ ሊያገኝ እንደሚገባው አመንን፡፡ ይህ ጥያቄ በቂ ምላሽ ኖሮት በአገልጋዩና በተገልጋዩ መሃል ግልጽ አሰራር እንዲኖር፣ ከሃሜት የፀዳ፣ በየትኛውም ቦታና ጊዜ ሊፈተሽ የሚችል አሰራር ያስፈልጋል፡፡ ለነዚህና ለመሰል ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡን ባለሙያ ጋብዘናል፡፡ አስተያየቱን የሰነዘሩት ተገልጋዮችም ሆነ ሌላው የህብረተሰብ ክፍል ለነዚህና ለመሰል መተማመንን ለሚያሰፍኑ ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት ስላለበት የፐብሊክ ሰራተኞች የትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት የትራንስፖርት ሥምሪት ንዑስ የሥራ ሂደት አስተባባሪ የሆኑት አቶ አማኑኤል ተዘራ የሰጡንን ምላሽ ይመልከቱ ዘንድ ተጋብዘዋልና ያንብቡን፡፡

 

“የትራንስፖርት አገልግሎት የመስመር ዝርጋታ በጥናት ላይ የተመሰረተ አይደለም” አንዳንድ ተገልጋዮች

አቶ አማኑኤል በቅድሚያ ይህን የሚያህል ትልቅ አገልግሎት ለማስጀመር መንግስት ሲያቅድ ስራው ሊሰራ የሚገባው በዕቅድና በጥናት ላይ ተመርኩዞ ሊሆን እንደሚገባው ማሰብ ብዙም የሚያስቸግር አይደለም፡፡ የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኛውን የትራንስፖርት ችግር በዘላቂነት ቀርፎ ተገልጋዩ ህዝብ ሊያገኝ የሚገባውን ሁሉ እገዛ እንዲያገኝ ታስቦ የተጀመረ ስራ በመሆኑ በተለይ አውቶብሶቹ ከየት ተነስተው ፣ በየት አልፈው ፣ የት ይሆናል መድረሻቸው የሚለውን ለመወሰን በርካታ ባለሙያዎችና በመስኩ ልምድ ያላቸው ግለሰቦች ተካፋይ የሆኑበት ጥናት ተደርጓል፡፡

በቅድሚያ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ አገልግሎቱን የሚፈልግበት ሰዓትና የጉዞ አቅጣጫ መነሻና መድረሻውን ማወቅ አስፈላጊ በመሆኑ የከተማዋን ዋና ዋና የመኖሪያ አካባቢዎችንና በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ ዋና የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት መስጫ መንገድ /ኮሪደሮች/ የመለየት ስራ ነው የሰራነው፡፡ አገልግሎት የምንሰጠው ለበርካታ የፌደራልና የአዲስ አበባ ከተማ ፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች በመሆኑ ለሁሉም አገልግሎት ለሚፈልጉ ተቋማት አንድ አንድ አውቶብስ የመመደብ አቅም ስለሌለን ልዋጭም ስላልሆነ በብዙሃን ትራንስፖርት መርህ መሰረት በአንድ አውቶብስ የተለያዩ ግን በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ሰራተኞችን በጋራ ማገልገል የምንችልበትን መንገድ ነው የተከተልነው፡፡ በዚህም መሰረት የሚኖሩበትን አካባቢ፣ የሚሳፈሩበትንና የሚደርሱበትን ቦታና አገልግሎቱ የሚሰጥበትን ሰዓት ማወቅ ስለነበረብን መረጃውን ለማግኘት የመረጃ ማሰባሰቢያ ቅጽ አዘጋጅተን ተቋማቱ ሞልተው እንዲልኩ ከማድረጋችን ባሻገር የየተቋማቱን የሰው ሃብት ልማት ኃላፊዎች በአገልግሎቱና በሚሰጡን መረጃ ላይ በስፋት መክረናል፡፡

በጥናታችን መሠረትም ከከተማዋ ዋና ዋና አካባቢዎች መካከል ሃያ ሰባት መነሻ ቦታዎችን በመለየትና የፌደራልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች መስሪያ ቤቶች በዋነኛነት የሚገኙባቸውን አስራ አንድ አካባቢዎችን መድረሻ ቦታዎች አደረግን፡፡ በቀጣይም የከተማዋን ዋና ዋና መንገዶችን በመከተል የአገልግሎት መስመር የዘረጋን ሲሆን አውቶብሶቹ በግልጽ የታወቀ መነሻና መድረሻ ሰዓት ፣ ተሳፋሪዎች የሚሳፈሩበትና የሚያወርዱበት ፌርማታ መወሰንና ለተጠቃሚዎቹ ማሣወቅ ቀጣዩ ስራችን ነበር፡፡ ከዚህም ባሻገር ተጠቃሚዎች ከዋና ዋና መድረሻ ቦታዎች ከአውቶብስ ወርደው ወደ ስራቸው በእግር በመጓዝ የሚገቡበትን ጊዜ ከ1 ኪሎ ሜትር ያነሰ ርቀት ታሳቢ አድርገን ነው፡፡ በሌላም መንገድ በቀላሉ ሊታወቁ የሚችሉ የአውቶቡስ ፌርማታዎችና ታክሲዎች የሚጠቀሙባቸውን ስፍራዎች የተለመደ ስያሜያቸውን እንደያዙ ቁጥር እንዲሰጣቸው ተደርጓል፡፡

በስተመጨረሻም ከየተቋማቱ ተጣርቶ የተላከውን የአገልግሎት ተጠቃሚ ሠራተኞች መረጃ በመስመር ቁጥር ፣ በፌርማታና በመድረሻ ኮድ በማድረግ መታወቂያ ወረቀት ለማዘጋጀት ፣ የአገልግሎት መስመሮችን አቅጣጫ ለመወሰንና ለመስመሮች የሚያሰፈልጉ አውቶብሶችን ቁጥር ለመወሰን ተጠቅመንበታል፡፡በአጠቃላይ እነዚህን ሁሉ ጥንቃቄዎች አድርገን ጥናት ላይ ተመርኩዘን ነው የመስመሮቹን ዝርጋታ ያደረግነው፡፡

አቶ አማኑኤል፡- ይሄ ጥያቄ በተለይ በተወሰኑ ወደ ስምሪቱ መነሻ አካባቢ ባሉ መስሪያ ቤት ሰራተኞች ተደጋግሞ ተነስቶ እኛም ደጋግመን መልስ ሰጥተንበታል፡፡ የኛ አውቶብሶች የሰርቪስ አገልግሎት የሚሰጡት ለአንድ መስሪያ ቤት ሰራተኛ ብቻ አይደለም፡፡ በአይነትም በስራ ባህሪይም የተራራቁ የተለያዩ መስሪያ ቤት ሰራተኞችን ነው፡፡ ከ168 በላይ ለሆኑ የፌደራል መስሪያ ቤቶች አገልግሎት እንሰጣለን፡፡ እንዲሁም ከ3000 በላይ በአዲስ አበባ አስተዳደር ስር ያሉ ጽ/ቤቶች ፣ ክፍለ ከተማዎች ፣ ወረዳዎች ፣ ሆስፒታሎች ፣ ትምህርት ቤቶችና የፖሊስ ተቋማት የአገልግሎታችን ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ የዚያኑ ያህል ወደ ስራ የመግቢያ ሰዓታቸው ይለያያል ለምሣሌ ያህል የጉምሩክ መስሪያ ቤት ሠራተኞች መምህራንና ሀኪሞች ወደ ስራቸው የሚገቡት ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ነው፡፡

ከዚህ ባሻገር ደግሞ የከተማችን የትራፊክ መጨናነቅ ሌላው ፈተና ነው፡፡ ጥቂት ደቂቃዎች ብናረፍድ አውቶቡሶቹ በትራፊክ መጨናነቅ ተያዙ ማለት ምን ያህል ሰራተኛ ከስራ ገበታው ላይ ሊቀር እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ ይህን ታሳቢ በማድረግ ነው እጅግ ርቀት ላላቸው መነሻ ቦታዎች ለምሣሌ ለአቃቂ መነሻ ሰዓት 12፡30 እንዲሆን የተወሰነው፡፡ የአብዛኞዎቹ መነሻ ግን 12፡45 አና አንድ ስዓት ነው፡፡ ሌሎች ሰርቪስ የሚሰጡ መስሪያ ቤቶች ለምሣሌ አየር መንገድና አንበሳ አውቶብስ ከየትኛውም አቅጣጫ መነሻቸው 12፡00 ስዓት ነው፡፡ በርግጥ ከመነሻው ጥቂት ራቅ ብለው ወደ ስራቸው የሚገቡ ሰራተኞች ከስራ ስዓታቸው ቀደመው ሊደርሱ ይችላሉ፡፡ በእኛ ግምት ውስጥ የምንከተው መድረሻ ቦታ ላይ ያሉ ሰራተኞች ስንት ሰዓት ይደርሳሉ የሚለውን ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር እኛ ሰራተኞችን በየመስሪያቤታቸው በር ላይ አይደለም የምንጥላቸው አማካኝ በሆነ ስፍራ ላይ ነው፡፡ አብዛኖቹ ከዋናው መንገድ ገባ ያሉ መስሪያ ቤት ሰራተኞች ወደ ስራ ገበታቸው ለመድረስ 10-15 ደቂቃ በእግራቸው ይጓዛሉ፡፡ ይህን ታሳቢ ማድረግ ግድ ስለሆነብን መነሻ ስዓት ስንወስን ይህን ግምት ውስጥ ከተናል፡፡

በስራ መውጫም ሰዓት እንደዚሁ ነው፡፡ የመንግስት የስራ ስዓት መውጫ 11፡30 ነው፡፡ ሁሉም ሰራተኛ ከመስሪያ ቤቱ ወደ አውቶብሶቹ መነሻ እስኪሚደርስ ያለውን ደቂቃ አስበን 11፡45 ነው አውቶብሶቹ የሚንቀሳቀሱት፡፡ በአጠቃላይ የጠዋቱም ሆነ የማታው የመነሻ ሰዓት ሁሉንም ሰራተኛ ያማከለ እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡ ይህ ችግር አሁን ያሉንን አውቶቡሶች ቁጥር ስንጨምር ትርጉም ባለው መልኩ የሚቀረፍ ይሆናል፡፡መንግስት ይህን አገልግሎት ለመስጠት ዋነኛ አላማ አድርጐ የተነሳው የመንግስት የስራ ስዓት ሳይሸራረፍ ሰራተኛው ከእንግልት ድኖ በአግባቡ የተመደበበትን ተግባርና ህዝብ የሰጠውን አደራ እንዲወጣ ነው፡፡ በዚህም በተሳካ ሁኔታ ስራችንን እየሰራን ነው፡፡ በርግጥ ይህን አስቸጋሪ ሁኔታ ካለመረዳት በተለያየ ጊዜ መሰል አስተያየቶችን እንሰማለን፡፡ የጥናትና የተግባራችን መነሻ ግን ይህ መሆኑን ዘርዝረን ስናስረዳቸው ብዙዎች ጥያቄያቸውን ያነሳሉ ብዙዎች ከእኔነት ስሜት ርቀው በጋራ እሳቤ ምላሹን ይቀበሉናል፡፡

“ባስ ካፒቴኖቻችሁ በሌሊት የሚያስነሱን የታክሲ አገልግሎት ሰጥተው ለሚያገኙት ኮሚሽን ሲሉ ነው” አንዳንድ ተጠቃሚዎች

የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች አገልግሎት የጀመርነው መስከረም 5 ቀን 2007 ዓ.ም ነው፡፡ የከተማ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት /የታክሲ/ የሙከራ መስመር እንኳን የጀመርነው ጥር 27 ቀን 2007 ዓ.ም ነው፡፡ እንግዲህ ቅድሚያ በመስከረም ለፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኞች አገልግሎት ስንሰጥ በሃያ ሰባቱም የመነሻ መስመሮች ቀደም ብዩ እንደገለፀኩት በጥናታችን መነሻነት የመነሻ ስዓቶችን ወስነን ነው፡፡ ወደ ከተማ ህዝብ አገልግሎት ስንገባ ይህ ሰዓት አልተለወጠም፡፡ የሰርቪስ አገልግሎታቸውን በአግባቡና በተወሰነው ሰዓት ከጨረሱ በኋላ ነው ወደ ህዝብ አገልግሎት የሚሰማሩት፡፡ ምቾትና አገልግሎቱ የተሟላ ከሁሉ በላይ ከአደጋ የተጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት ነው ትኩረት ሰጥተን የገባነው፡፡ ለካፒቴኖቻችን የማበረታቻ ገንዘብ የሚከፈለው በተወሰነለት ሰዓት የፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኛውን አገልግሎት መስጠቱን ካረጋገጥን በኋላ ነው፡፡ እነዚህ አውቶብሶች ደግሞ የሁሉም ህዝብ ንብረቶች ናቸው፡፡ለሠራተኞች አገልግሎት ከሠጡ በኋላ አውቶቡሶቹ በየአደባባዩ ተኮልኩለው ቆመው ህዝቡ በትራንስፖርት እጥረት ሲንገላታ ማየት በማንኛውም መመዘኛ ተቀባይነት ያለው አይመስለንም፡፡ የትራንስፖርት ችግር ከጊዜ ወደጊዜ እየተበራከተ በመጣበት ሁኔታ ሌላውንም ህዝብ የማገልገል ተቋማዊ ግዴታ አለብን፡፡ ሁሉም የኔነት ስሜት እንዲፈጠርበት እንፈልጋለን፡፡ከዚህ በተረፈ ለፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኛው የሚሰጠውን አገልግሎት የሚቆጣጠሩ እኛ በስውርም በግልጽም ከምናሰማራቸው አባሎቻችን ባለፈ ከተጠቃሚው መካከል የሚመረጡ አስተባባሪዎች አሉ፡፡ እነዚህ አስተባባሪዎች ባስ ካፒቴኖቻችን በሰዓታቸው ከመነሻቸው መነሳታቸውን፣ የተዘረጋላቸውን መሰመር ጠብቀው ሰራተኛውን መጫናቸውን፣ ህግን አክብረው መጓዛቸውንና የመኪኖቻቸውን ንጽህና ባግባቡ መቆጣጠራቸውን እየተከታተሉ ሪፖርት ያደርጉልናል፡፡ በርግጥ መስተካከል ያለበት ችግር ካለ አፋጣኝ እርምጃ እንወስዳለን፡፡ እስካሁን ግን በጐላ ሁኔታ “የታክሲ ስራ ለመስራት ሲሉ ያለሰዓታቸው ይሄዳሉ፡፡” የሚል ሪፖርት አልደረሰንም፡፡

“የመነሻ ሰዓት በቀጣይ ሊስተካከል ይገባዋል” አንዳንድ ተጠቃሚዎች

“በርግጥ ይገባዋል፡፡ ይህ ግን አቅምን የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ አቅደን ከገባንበት የአውቶብሶች ቁጥር አሁን እየሰራን ያለነው በግማሽ ያህሉ ነው፡፡ ምን አልባት በቀጣይ የተሻለ ቁጥር አውቶብሶችን ስናስገባ አጫጭር መስመሮችን ዘርግተን የቅርብ የቅርቦቹን ሰዓት ለማሻሻል እንችል ይሆናል፡፡ አሁን ባለን አገልግሎት ግን ብዙዎች የከተማ የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ከሚሰጡ አውቶብሶች የኛ ሰዓት የተሻለ ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት አገልግሎት ከሚጀመሩበት ቦታ የኛ የራቀ ነው፡፡ ለምሣሌ ብዙዎች ከቃሊቲ አያልፉም እኛ ግን ከአቃቂ እንነሳለን ፣ ጥቂት የማይባሉት ደግሞ ከአየር ጤና ነው አገልግሎት የሚጀመሩት እኛ ግን ካራ ቆሬ ፣ አለምባንክ ገብተን ነው ተገልጋዩቻችንን የምንወስደው፡፡ አሁንም ብዙዎች ኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ነው መነሻቸው እኛ ግን ካራ ሌሎች ደግሞ ከአያት ይጀምራሉ የኛ መነሻ ግን ጨፌ አያትና የካ አባዶ መግቢያ ድረስ እንዘልቃለን፡፡ ከዚህ መነሻነትና የከተማዋን የትራፊክ ጭንቅንቅ ግምት ውስጥ ባስገባ ጥናት ነው ሰዓታችንን በጣም ርቀት ያላቸውን ጥቂት መስመሮች መነሻቸውን 12፡30 አድርገን አብዛኞቹን 12፡45 እና 1፡00 ያደረግነው፡፡መንግስት ካለው ውስን የኢኮኖሚ አቅም ለዜጐች ይህን አስቦ በሰለጠኑት አለማት እንኳን ባልተሞከረ ሁኔታ ለፐብሊክ ሰርቪስ ሰራተኛው ለህዝቡ አገልግሎት እየሰጠ ያለው ወደፊት ሀገራችን ያሰበችው ሲሳካ ከዚህ የተሻለ ሰርቪስ የማይሰጥበት ሁኔታ አይኖርም፡፡ ሳይደላው ይህን ያደረገ መንግስት ይበልጥ አቅም ሲኖረው የተሻለ የማያደርግበት ምክንያት እንደማይኖር ለሁሉም ግልጽ ነው፡፡                        

 

comments